ሦስተኛ የኢትዮ -ሞሮኮ በዚነስ ፎረም ተካሄደ

ሦስተኛ የኢትዮ -ሞሮኮ በዚነስ ፎረም ተካሄደ

ሶሥተኛው ኢትዮ-ሞሮኮ ቢዝነስ ፎረም ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

በዚህም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የኢትዮጵያና የሞሮኮ ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን ፎረሙ የሁለቱን አገራት የንግድ ፣ የኢንቨስትመንት እና የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሚያሳድግ ይታመናል።

የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስትር ዶ/ር በቀለ ጉላዶ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ያላት ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ፣የተፈጥሮ ሀብት፣ ሰፊ የሰው ኃይልና የተረጋጋ ኢኮኖሚ በመጠቀም የሞሮኮ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

አንጻራዊ ርካሽ የአሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት፣ ለዓለም ገበያ ያላት ቅርበትና ሰፊ የገበያ አማራጮች ኢትዮጵያን በባለሃብቶች ዘንድ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እያደረጋት እንደሚገኝም ዶ/ር በቀለ ተናግረዋል።

የሞሮኮ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣በማዕድን እና ኢነርጂ ዘርፎች ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑም አስረድተዋል።

የሞሮኮ የንግድ ፣ኢንቨስትመንት እና ኢንዲስትሪ ሚኒስቴር ዋና ተጠሪ ረቂያ ኤዲርሃም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሞሮኮ ስትራቴጅክ አጋር እና የምስራቅ አፍሪካ መግቢያ በር ናት ብለዋል።

ሞሮኮ “የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብት ለአፍሪካ እድገት እና የጋራ ብልፅግና” በሚል መርህ እየሰራች እንደሆነም ተጠሪዋ ተናግረዋል።

በሞሮኮ ባለሃብቶች በ2.5 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ የሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካን ለአብነት ጠቅሰው በቀጣይ ሁለቱ አገራት በንግድ እና ኢንቨስትመንት ያላችውን ትብብር የበለጠ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በፎረሙ ላይ ከሁለቱ አገራት የተውጣጡ በተለያዩ ዘርፍ የተሠማሩ 110 ኩባንዎች የተሳተፉ ሲሆን የቢዝነስ ለቢዝነስ ውይይት እና ትስስር ተደርጓል።

ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያሳይ ገለጻም ለፎረሙ ተሳታፊዎች ተደርጓል።

ጥቅምት 16/2010 /የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *