ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ኮከብ ፈፃሚ ተብላ ተሸለመች

 

አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2010 ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ኮከብ ፈፃሚ ተብላ ተሸለመች።
ሽልማቱን ያገኘችው የዓለም ባንክ በኦስትሪያዋ ቪየና ከተማ ትናንት ባካሄደው የኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነት ፎረም ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ፖሊሲና አሰራር ማሻሻያዎች ትግበራ ከበርካታ አገራት ጋር ተወዳድራ የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገቧ የ”ስታር ሪፎርም አዋርድ” ሽልማትን ተቀዳጅታለች።
ሽልማቱን በዶክተር አርከበ እቁባይ የተመራው ልዑክ በስፍራው በመገኘት ተቀብሏል።
የሽልማቱ ዋና ዓላማ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች መንግስታት በወሰዷቸው ቁርጠኛ ተግባራት በሽግግር ሪፎርሞች የተመዘገቡ ስኬቶችን ማበረታታት እንደሆነ ባንኩ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ባከናወነቻቸው ተግባራት የአገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ከዓለም ባንክ አድናቆት ተችሯታል።
ባንኩ ዘርፉን በሚመለከት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጾ፤ አገሪቱ በፈረንጆቹ 2025 የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማዕከል የመሆን ራዕይ ለማሳካት በትክክለኛ መንገድ እንደምትገኝ ማስገንዘቡም በመግለጫው ተመላክቷል።

መንግስት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ያቀደውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት በቁርጠኝነት በመንቀሳቀሱ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ የተለያዩ እውቅናዎችን ማግኘቱም ተጠቁሟል።
መሰረተ ልማት ያካተቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋትና አገሪቱን ለኢንቨስትመንት ምቹ መዳረሻ ለማድረግ በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ የማበረታቻ ድጋፎች ኢትዮጵያን በዋናነት ተሸላሚ እንድትሆን እንዳስቻሏትም ተገልጿል።
የአገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ46 በመቶ ብልጫ አንዳስመዘገበም ተብራርቷል።
ይህም አገሪቱ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ቀዳሚ ከሆኑ የአፍሪካ አገራት አንዷ እንድትሆን አስችሏታል።
በፎረሙ ከፍተኛ የፖሊሲ አውጪዎች፣ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶችና ተመራማሪዎች መገኘታቸው ታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *