የደች የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ቁራዎች በየመንገዱ የሚጣሉ የሲጋራ ቁራጮችን እንዲያፀዱ ለማሰልጠን አቅደዋል

የደች የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ቁራዎች በየመንገዱ የሚጣሉ የሲጋራ ቁራጮችን እንዲያፀዱ ለማሰልጠን አቅደዋል።
ሩቤን ቫን ዴር ቨሌውተን እና ሮብ ስፓይክማን የተባሉት ሁለቱ ባለሙያዎች በአምስተርዳም ጎዳናዎች የሲጋራ ቁራጮችን ለማፅዳት አዲስ ሃሳብ አፍልቀዋል።ከዚህ በፊት ሮቦቶችን በመጠቀም መንገዶችን ፅዱ ለማድረግ ቢያቅዱም፥ በሮቦት የቴክኖሎጂ ስራ ብቻ የሲጋራ ቁራጮችን በየመንገዱ እና ጥጋጥጉ ማስወገድ እንደማይቻል ይረዳሉ።
ይህን እንዳወቁም እቅዳቸውን ለውጠው በከተሞች አካባቢ ብዙ ያልተለመዱትን አዕዋፋትን ለማሰልጠን ወሰኑ።
ከአዕዋፋት መካከል በማንኛውም ከተማ የመገኘት እድል ያላቸውን እርግቦች ለመጠቀም ፈልገው ነበር።
ሆኖም የእርግቦች ስልጠናውን የመቀበል ያን ያህል በመሆኑ ሀሳባቸውን ቀየሩ።
ሁለቱ ሀሳብ አመንጪዎች ከአዕዋፋት መካከል “ቁራ” የሚባለው ጥቁር የወፍ ዝርያ ለፈለጉት ዓላማ መሳካት ወሳኝ ሆኖ አገኙት።
ቁራ በዓለም ላይ ካሉ ፍጥረታት በንቃት እና አዕምሯዊ ልህቀታቸው ከፍተኛ ደረጃ ከሚባሉት ይሰለፋል።
እነ ስፓይክማን የቁራ ነገሮችን የመመርመር እና የመላመድ አቅሙ ከዝንጀሮ ዝርያዎች ጋር እኩል ሆኖ በማግኘታቸው ለፕሮጀክታቸው እውን መሆን ተማምነውበታል።
ለዚህ መሳካትም የቁራ ሳጥን ወይም (crow box) የተሰኘች የማሰልጠኛ ማሽን ሰሩ።
ማሽኗ ቁራዎች በየመንገዱ ዳርቻ የሲጋራ ቁራጮችን በየጊዜው ማንሳት የሚያስችለውን ስልጠና ለመስጠት የምታገለግል ናት።
በስልጠናውም ሳህን መሳይ ማሽኗ የሲጋራ ቁራጭ እና የቁራ ምግብ አምሳስሎ በአንድ ላይ ለማስቀመጥ እና ውጤቱን ለመመዝገብ ዓላማ ነው የዋለችው።
በዚህም መሰረት ቁራዎች የሲጋራ ቁራጮችን እያነሱ ወደ ተፈለገው የማክማቻ ሳጥን ውስጥ እንዲያስገቡ የሚያግዝ የሙከራ ስልጠና ይወስዳሉ።
ሙከራው ካለቀ በኋላም ሙሉ ስራው ይጀመራል ተብሏል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት በየዓመቱ 6 ትሪሊየን ሲጋራዎች የሚጨሱ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ ሶስት አራተኛ ያህሉ ማረፊያቸው በአካባቢ ላይ ነው።
ይህም ማለት 4 ትሪሊየን የሲጋራ ቁራጮች በጥንቃቄ የማይቀመጡ በመሆናቸው ለአካባቢ ብክለት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው።
ለማሳያነትም 2 ነጥብ 5 ሚሊየን የኦሊምፒክ የመዋኛ ገንዳዎችን ከጥቅም ውጭ አድርጎ ለመሙላት 4 ትሪሊየን የሲጋራ ቁራጮች በቂ መሆኑን ተመራማሪዎች ያነሳሉ።
ታዲያ ደቻውያኑ ባለሙያዎች ይዘውት የመጡት ሲጋራን ከመንገዶች የማፅዳት ውጥን የሚበረታታ ሲሆን፥ በጥንቃቄ መተግበር ይኖርበታልም ተብሏል።
አንዳንድ ተመራማሪዎች እንዲያውም ቁራዎች በሰዎች አካባቢ እየዞሩ የሲጋራ ቁራጮችን ሲያነሱ የምናይበት ጊዜ መምጣቱ የሰው ልጅ ለራሱ ግድ የለሽ የሆነበት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ይሆናል እያሉ ነው።


 

ምንጭ፦FBC ኦዲቲ ሴንትራል ጠቅሶ እንደገለፀው

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *