አዋሽ ኢንሹራንስ የግል ኢንዱስትሪውን ሲመራ ኅብረት ኢንሹራንስ በ70 ሚሊዮን ብር ይከተላል

አዋሽ ኢንሹራንስ የግል ኢንዱስትሪውን ሲመራ ኅብረት ኢንሹራንስ በ70 ሚሊዮን ብር ይከተላል
አዋሽ ኢንሹራንስ የግል ኢንዱስትሪውን ሲመራ ኅብረት ኢንሹራንስ በ70 ሚሊዮን ብር ይከተላል

በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከ22 ዓመታት በላይ የዘለቀው አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ በ2009 ዓ.ም. ከአገሪቱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአረቦን ገቢና በትርፍ መጠን ለአምስተኛ ጊዜ ቀዳሚ ለመሆን እንደቻለ ገለጸ፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ በበኩሉ የ70 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝቧል፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ የዓምናው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ እንደሚያሳው፣ ከታክስ በፊት 101.7 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ እንዳገኘ፣ የተጣራ ትርፉን በ31.5 በመቶ በማሳደግ 88 ሚሊዮን ብር ሊያደርስ ችሏል፡፡ የኩባንያውን የአረቦን ገቢ አሰባሰብ በተመለከተ መግለጫው እንዳመለከተው፣ ከጠቅላላ የመድን ሥራ የ544.6 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ለመሰብሰብ ችሏል፡፡ የዚህ ዘረፍ የአረቦን ገቢው ካቻምና ከሰበሰበው ይልቅ የ14 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በሕይወት መድን ሥራ ዘርፍም 55.1 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን አስታውቋል፡፡ በሕይወት መድን ዘርፍ ያሰባሰበው አረቦን ከካቻምናው የ22 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ተጠቅሷል፡፡ ኩባንያው ከጠቅላላው የመድን ሥራና ከሕይወት መድን ዘርፍ ያሰባሰበው የአረቦን ገቢ በአገሪቱ የመድን ኢንዱስትሪ ውስጥ ከግል ኩባንያዎች አኳያ ለአምስተኛ ጊዜ ቀዳሚ በመሆን ዘርፉን እንዲመራ እንዳስቻለው ኩባንያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ በጠቅላላ የመድን ዘርፍ ብቻ 238.6 ሚሊዮን ብር ካሳ እንደከፈለም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኩባንያው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋለ ንዋይ ያፈሰሰ ሲሆን፣ ከኢንቨስትመንቶቹም ጠቀም ያለ የትርፍ ድርሻ ማግኘቱን አመላክቷል፡፡ በ2009 ዓ.ም. በአዋሽ ባንክ ከያዘው የአክሲዮን ድርሻ የ27.4 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት መቻሉን አመልክቷል፡፡ በቅርቡም ኦዳ አክሲዮን ማኅበር ከተሰኘውና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከተቋቋመው ኩባንያ የ3.5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖችን የገዛ ሲሆን፣ ግንባታው የተጀመረው የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የስብሰባና የኤግዚቢሽን ማዕከልን ዕውን እንደሚያደርግ ከሚጠበቀው አክሲዮን ማኅበር 409 ሺሕ አክሲዮኖችን እንደገዛ አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር፣ በ2009 ዓ.ም. ከነበረው እንቅስቃሴ የገበያ ድርሻውን ቢያሰፋም፣ ያገኘው የትርፍ መጠን በ2008 ዓ.ም. ካስመዘገበው ያነሰ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

የኅብረት ኢንሹራንስን የ2009 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም የሚያሳየው ሪፖርት፣ በገበያ ድርሻ፣ በአረቦን ገቢ መጠን፣ በካፒታልና በመሳሰሉት ረገድ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ይሁን እንጂ ዓምና ሊያገኝ የቻለው የ70 ሚሊዮን ብር የትርፍ መጠን ግን ከካቻምናው ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የኅብረት ኢንሹራንስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢና የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ እንደገለጹት፣ ኩባንያው ካስመዘገበው የአረቦን ገቢና የገበያ ድርሻ ዕድገት አንፃር ሲታይ፣ በ2009 ዓ.ም. የተገኘው ትርፍ ከ2008 ዓ.ም. አኳያ ያነሰ ሆኗል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ግን በ2009 ዓ.ም. ከፍተኛ የካሳ ጥያቄ መቅረቡ ነው፡፡ እንደ አቶ ግርማ ገለጻ፣ ኩባንያው ለወደፊት የላቀ ገቢ እንደሚያስገኙ በሚታመንባቸው ድርጅቶች ውስጥ ያካሄደው የኢንቨስትመንት መጠንና የሚያስገኘው የትርፍ ድርሻ ገቢ (ዲቪደንድ)፣ ከኅብረት ባንክ ከተገኘው በቀር የተጠበቀውን ያህል ባለማስገኘታቸው ላስመዘገበው የትርፍ ቅናሽ ሌላው ምክንያት ተደርጓል፡፡ ለሕንፃ ግንባታዎች ከፍተኛ ወጪ መውጣቱ፣ ግንባታው የተጠናቀቀውና ቃሊቲ አካባቢ የሚገኘው የኩባንያው ሕንፃ የሚጠበቀውን ያህል የኪራይ ገቢ አለማስገኘቱም ለትርፉ ማነስ የሚጠቀሱ ምክንያቶች እንደሆኑ አቶ ግርማ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡

በኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት በ2009 ዓ.ም. ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ዘርፍ 387 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ከሕይወት ነክ የመድን ዘርፍ የ29.8 ሚሊዮን ብር፣ በጠቅላላው የ417 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ሰብስቧል፡፡ ይህም በ2008 ዓ.ም. ከተገኘው የአረቦን ገቢ ጋር ሲነፃፀር ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ዘርፍ 23 በመቶ፣ ከሕይወት መድን ዘርፍ ደግሞ የአሥር በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል፡፡ ‹‹ኩባንያችን በሒሳብ ዓመቱ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በተለይም ባለፉት ዓመታት የታየውን የገበያ ድርሻ ማዘቅዘቅ ለመቀልበስና የገበያ ድርሻችንን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ቀድሞ ከነበረው የ5.20 በመቶ ወደ 5.43 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል፤›› ያሉት አቶ ግርማ፣ የተጠናቀቀው ዓመት ካለፉት አምስት ዓመታት በተሻለ መንገድ በሁሉም የኢንሹራንስ ዘርፎች የገቢ ዕድገት እንደታየ አስታውቀዋል፡፡

ኅብረት ኢንሹራንስ በ2009 ዓ.ም. አንድ ቅርንጫፍና ስድስት አገናኝ ቢሮዎችን ከፍቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኢንዱስትሪው ውስጥ አዳዲስ የሆኑትን እንደ የድንገተኛ ሕክምና ኢንሹራንስ፣ በፖለቲካ አመፅና በሽበርተኝነት ለሚደርሱ ጉዳቶች የመድን ሽፋን እንዲሁም በተወሰኑ የመድን ዘርፎች የኢንተርኔት ሽያጭ በመዘርጋት ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎቶችን እያቀረበ ተደራሽነቱን በማሳደግ ፈር ቀዳጅ ለመሆን ችሏል ተብሏል፡፡

ቸርቸል ጎዳና፣ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ በመገንባት ላይ የሚገኘው የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በ2010 ዓ.ም. አጋማሽ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አቶ ግርማ አስታውቀዋል፡፡ ሕንፃው ሲጠናቀቅ የዋናው መሥሪያ ቤት ቢሮ ወደዚያው የሚዛወር ሲሆን፣ ለዋናው መሥሪያ ቤት የቢሮ ኪራይ ሲወጣ የቆየውን ወጪ ከማስቀረት ባሻገር፣ በአዲሱ ሕንፃ ከኪራዩ ቤቶች ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡ በቃሊቲ አካባቢ ላስገነባው፣ የግንባታ ሒደቱ እየተጠናቀቀ ለሚገኘው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ እስካሁን በድምሩ ከ320 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አውጥቷል፡፡

ኩባንያው በራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ የ12 ሚሊዮን ብር፣ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር የ12.5 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ የአምስት ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ኢንቨስትመንቶች በማካሄድ አክሲዮኖችን እንደገዛ አስታውሰዋል፡፡ ኢንቨስትመንቶቹ ወደፊት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኙ ቢታመንም፣ ባለፈው ዓመት ግን ከእነዚህ ኢንቨስትመንቶች የተገኘ የትርፍ ድርሻ ገቢ እንዳልነበር ተገልጿል፡፡

አዋሽ ኢንሹራንስ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 44 ያደረሰ ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉም 246.6 ሚሊዮን ብር አድርሷል፡፡ ከ23 ዓመታት በፊት 456 የነበሩት የባለአክሲዮኖች ቁጥር፣ በአሁኑ ወቅት 1254 እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስም በአሁኑ ወቅት ያስመዘገበውን የተከፈለ ካፒታል መጠን 245.07 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ችሏል፡፡

ምንጭ-ሪፖርተር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *