ኢንስቲትዩቱ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአካቶ ትምህርት ስልጠና ሊጀምር ነው

ኢንስቲትዩቱ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአካቶ ትምህርት ስልጠና ሊጀምር ነው

አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአካቶ ትምህርት ስልጠና ሊጀምር መሆኑን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ በማድረግ የአካቶ ትምህርት ስልጠናን መተግበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር መክሯል።

የፊንላንድ መንግስት ለአካቶ ትምህርት ስልጠና ፕሮግራሙ የ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ፕሮጀክቱ ለሶስት ዓመት የሚቆይ ነው።

ከአገሪቷ ህዝብ መካከል 17 በመቶ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች ናቸው።

በመሆኑም የስርዓተ ትምህርት ክለሳ በማድረግ አካል ጉዳተኞችን በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተጠቃሚ የሚያደርግ የአካቶ ትምህርት ስልጠና ፕሮጀክት ተቀርጿል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳህለስላሴ ተካ እንደገለጹት የትምህርትና ስልጠና ስርዓቱን የመቀየርና ስርዓተ ትምህርቱን በመከለስ የአካቶ ስልጠናውን በሚመልስ መልኩ የማዘጋጀት ስራ ይሰራል።

ቀደም ሲል የነበረው የቴክኒክና ሙያ ስርዓተ ትምህርት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ክፍተት እንደነበረበት ገልጸው በፊንላንድ መንግስትና በኢንስቲትዩቱ ትብብር እነሱን አካቶ በማሰልጠን ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በፕሮጀክቱ የፊንላንዶቹ ጃምክ መምህራን ኮሌጅና በጅቫስኪላ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የቴክኒክና የስልጠና ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ከፊንላንድ ጃምክ መምህራን ኮሌጅ የመጡት የፕሮጀክቱ ማኔጀር ዶክተር ማያ ሂርቮኔን አካል ጉዳተኞችን በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አሰማርቶ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ሰፊ ክፈተቶች ይታያሉ ብለዋል።

በመሆኑን የአገራቸው መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከኢንስቲትዩቱ ጋር የአካቶ ስልጠና ለመጀመር የሶስት ዓመት ፕሮጀክት ቀርጾ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የፊንላንድ መንግስት ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ የስልጠናና የቴክኒክ ድጋፎች እንደሚያደርግም ገልጸዋል ዶክተር ማያ።

ምንጭ /ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *