የምርምርና የፈጠራ ስራ ውድድር ኤግዚቪሽን መካሄድ ጀመረ

የምርምርና የፈጠራ ስራ ውድድር ኤግዚቪሽን መካሄድ ጀመረ

የኢ.ፌ.ዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሂሳብና ሣይንስ ትምህርቶች ማሻሻያ ማዕከል ከስቴምስ ሲነርጂ ፣ከዩኔስኮ እና ከኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ጋር በመተባበር “በሣይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ የበለፀገ ህብረተሰብ ለዘላቂ ሠላምና ልማት “በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የምርምርና ፈጠራ ስራ ውድድር ኤግዚቪሽን በኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የምርምርና የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ መከፈት አስመልክቶ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ የኢትዮጵያን ሣይንስ ለማበልፀግ የተቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ የህብረተሰቡን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲሁም ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅሙን ለማጎልበት ለማስተማርና የሣይንስ ፖርሽን ለመፍጠር የተሰራ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ ቋሚ የሳይንስ ማዕከል ለመፍጠር ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ፡፡
በዚህም ወጣቱ ወደ ሣይንስ በሄደ ቁጥር የሀገራችን ተስፋ እየለመለመ ይሄዳል ብለዋል፡፡

ስለ ፕሮግራሙ አላማና አስፈላጊነት አጭር ንግግር ያደረጉት በትምህርት ሚኒስቴር የሂሳብና ሣይንስ ትምህርቶች ማሻሻያ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በላይነህ ተፈራ ሲሆኑ የዚህ የምርምርና የፈጠራ ስራ ውድድር አውደ ርዕይ በአለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ህዳር 1 ቀን የሚከበረውን የአለም የሣይንስ ቀን በማስመልከት በአገራችን ለ2ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን ተማሪዎችን ለማነሳሳትና ለማብቃት የተዘጋጀ ነው ፡፡

በፕሮግራሙ የእውቀትና የክህሎት ሽግግር እንዲሁም የልምድ ልውውጥ በማድረግ ተማሪዎች ለሂሳብና ሣይንስ ትምህርቶች ያላቸውን ግንዛቤ ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የምርምርና የፈጠራ ስራ ውድድር ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ክልል ትምህርት ቢሮ ድረስ ሲካሄድ ቆይቶ የተሻለ የፈጠራ ስራ ያላቸው ተማሪዎች ከሁሉም ክልል የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የተመረጡ በዚህ አውደርዕይ የፈጠራ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በነገው እለትም የቀረቡት የፈጠራ ስራዎች በኮሚቴ አማካኝነት በተዘጋጁ መስፈርቶች መሰረት የማወዳደር ስራ ሲካሄድ ይቆይና ከጥቅምት 29 – 30/ 2010 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ለህዝብ እይታ ክፍት እንደሚሆኑ በጠቆም ህብረተሰቡ ጉለሌ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ የሣይንስ ማዕከል በመገኘት እንዲጎበኝና የተማሪዎቹን የፈጠራ ውጤቶች እንዲያበረታቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ይህ የምርምርና የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 01/ 2010 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ጥቅምት 27/ 2010/የትምህርት ሚንስቴር/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *