ዳሸን ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት አዲስ መሥሪያ ቤት ገነባ

ዳሸን ባንክ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት አዲስ መሥሪያ ቤት ገነባ

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪውን መቀላቀል ከቻሉ ቀደምት የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ዳሸን ባንክ፣ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ያወጣበትን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ያስመረቀው ሕንፃ 21 ወለሎች ያሉት ሲሆን፣ በውስጡ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎችን አካቷል፡፡ ከባንኩ ምሥረታ ጀምሮ በቅሎ ቤት አካባቢ በዋና መሥሪያ ቤት ሲገለገልበት የቆየውን ሕንፃ በመልቀቅ ወደ አዲሱ ሕንፃ በቅርቡ እንደሚዛወርም አስታውቋል፡፡

በ2,690 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውና 35,145 ካሬ ሜትር የወለል ስፋት ያለው ይህ ሕንፃ፣ አምስት መደበኛ፣ ሁለት የቪአይፒና አንድ የጭነት አሳንሰሮችን በማካተት በጠቅላላው ስምንት አሳንሰሮች እንደተገጠሙለት ዳሸን ባንክ ለሪፖርተር ከላከው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሁለት የስብሰባ አዳራሾች፣ የሠራተኞች መመገቢያ፣ ክሊኒክ፣ የሕፃናት ማቆያ፣ ጂምናዝየም፣ የባንኩ የታሪክ መዘክርን ጨምሮ ከ170 በላይ መኪኖች ማቆም የሚያስችል ሥፍራን ያካተተተ ግንባታ እንደተከናወነ ባንኩ አስታውቋል፡፡ ከሕንፃው በታች በምድር ውስጥ ያሉ ሦስት ወለሎች ለመኪና ማቆሚያ ታስበው የተገነቡ ናቸው፡፡

ሕንፃው ዘመናዊ የአየር እንቅስቃሴ፣ የሰነድ አያያዝና የኤሌክትሪክ ኃይል ዝርጋታና አጠቃቀም ሥርዓት የተገጠመለት ሲሆን፣ ቦታ ቆጣቢ፣ ለሥራ አመቺና የሠራተኞችን የሥራ ላይ ደኅንነት ለመጠበቅ በሚያስችሉ የቢሮ መገልገያዎችና ቁሳቁሶች በቅርቡ እንደሚደራጅ ተጠቅሷል፡፡

ከፍተኛ ሀብት ለማካበት ከበቁ ከአገሪቱ ሦስት ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ዳሸን ባንክ፣ በአዲስ አበባ ካስገነባው ዘመናዊ መሥሪያ ቤት ባሻገር፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የራሱ 24 ሕንፃዎች ባለቤት ለመሆን የበቃ ተቋም ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ከሚገኙ የባንኩ 330 ቅርንጫፎች ውስጥ 24ቱ የሚገኙት በባንኩ የግል ሕንፃዎች ውስጥ ነው፡፡

ዳሸን ባንክ ከ21 ዓመታት በፊት የተቋቋመው በ14 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ያከማቸው ካፒታል መጠን ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት የሚያሳየው የባንኩ መረጃ የባንኩን ተቀማጭ የገንዘብ መጠን ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ሊያደርሱት እንደቻሉ ይጠቁማል፡፡ ከሰባት ሺሕ በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድረው ይህ ባንክ፣ የካርድ ባንኪንግ አገልግሎትን ቀድሞ በመጀመርም ይታወቃል፡፡

አዲሱን የዳሸን ባንክ ሕንፃ የገነባው ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ሲሆን፣ የሕንፃውን ዲዛይን ደግሞ ኃይለ ገብርኤል ኮንሰልቲንግና አርክቴክት ኢንጂነሪንግ የተሰኘው አገር በቀል ኩባንያ አዘጋጅቶታል፡፡ ዳሸን ባንክ በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ የትርፍ መጠኑን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማድረስ ከግል ባንኮች አዋሽ ባንክን በመከተል ሁለተኛው ባንክ በመሆን የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን በቀዳሚነት ከሚመሩት አንዱ ነው፡፡

ምንጭ- ሪፖርተር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *